የዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድ ገቢ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ሆነ

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ፡፡

ይህ ገቢ በዕቅድ ተይዞ ከነበረው 3.6 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር 57 በመቶው ብቻ እንደተሳካ ታውቋል፡፡

በተጨማሪም ካለፈው ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ4.3 በመቶ (100 ሚሊዮን ዶላር) ብቻ ጭማሪ ተመዝግቧል፡፡ አብዛኛው ገቢ ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ከግብርናው ዘርፍ የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው ከማኑፋክቸሪንግና ከማዕድን ዘርፍ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ከግብርናው ዘርፍ ለዘጠኝ ወራት ከታቀደው ገቢ 2.38 ቢሊዮን ዶላር 1.58 ቢሊዮን ዶላር የተሳካ ሲሆን፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው 332.54 ሚሊዮን ዶላር በማስገባት ከዕቅዱ 49.2 በመቶውን ብቻ ማሳካቱ ታውቋል፡፡

ዝቅተኛ የሆነ አፈጻጸም ያስመዘገበው የማዕድን ዘርፍም 109.82 ሚሊዮን ዶላር ወይም 20 በመቶ ብቻ አስገኝቷል፡፡ ለዚህም ምክንያት የሆነው የኮንትሮባንድ ገበያ በማዕድን ዘርፍ ችግር በመፍጠሩ ነው፡፡ ለገቢው አለማደግ ምክንያት ኮንትሮባንድ ነው ሲሉ የንግድ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ወራት በዓመቱ የታቀደውን 4.663 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከወጪ ንግድ ለማሳካት ያሉትን ክፍተቶች ለማሟላት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡